ኤርትራ ሠራዊቷን በአስቸኳይ ከግዛቷ እንድታስወጣ እና ለድርድር ዝግጁ እንድትሆን ኢትዮጵያ ጠየቀች
Author
amc-admin
Date Published

ኤርትራ ሠራዊቷን በአስቸኳይ ከግዛቷ እንድታስወጣ እና ለድርድር ዝግጁ እንድትሆን ኢትዮጵያ ጠየቀች
የኤርትራ ሠራዊት ተቆጣጣሯቸዋል ካላቸው የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛቶች እንዲወጣ እና ለድርድር ዝግጁ እንዲሆን የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጠየቀ።
ሚኒስቴሩ ቅዳሜ ጥር 30/2018 ዓ.ም. ለኤርትራው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጻፈው ደብዳቤ ላይ ኤርትራ የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ድንበር በመጣስ በሰሜን ምሥራቅ አቅጣጫ የሚገኙ አካባቢዎችን ተቆጣጥራ እንደምትገኝ ገልጿል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው የደብዳቤውን ትክክለኛነት ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
ደብዳቤው የኢትዮጵያ መንግሥት በተደጋጋሚ የኤርትራ ጦር ከግዛቱ ለቅቆ እንዲወጣ መጠየቁን አስታውሶ፤ ይህ ጥያቄው ተቀባይነት የሚያገኝ ከሆነ "የባሕር አገልግሎት ጉዳዮችን እና በአሰብ ወደብ በኩል የባሕር መዳረሻን ጉዳይ ጨምሮ ሁሉንም የጋራ ጥቅም ጉዳዮችን ለመፍታት በቅን ልቦና በድርድር ለመሳተፍ ፈቃደኛ" መሆኑን አስታውቋል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) የተጻፈው እና ለኤርትራው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳላህ በተላከው በዚህ ደብዳቤ፣ የኤርትራ ሠራዊት "ለረዥም ጊዜ" የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ግዛት በመጣስ በሰሜን ምሥራቅ አቅጣጫ ተቆጣጥሮ እንደሚገኝ ተጠቅሷል።
በዚሁ ደብዳቤ ላይ ሁለቱ አገራት በሚያዋስናቸው አካባቢዎች የኤርትራ መንግሥት በስም ላልተጠቀሱ የተለያዩ ታጣቂ ቡድኖች "ቀጥታ የቁሳቁስ ድጋፍ እና እርዳታ" እንደሚያቀርብ በመጥቀስ ወንጅሏል።
በደብዳቤው ላይ የታጣቂ ቡድኖቹ በስም ባይጠቀሱም ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ መንግሥት ኤርትራ ለህወሓት እና ለፋኖ ታጣቂዎች ድጋፍ ያደርጋል ሲል መወንጀሉ ይታወሳል።
ኢትዮጵያ በደብዳቤው ላይ የኤርትራ መንግሥት በሉዓላዊነቱ እና በድንበር ላይ ከሚፈጽመው ጥሰት በተደጋጋሚ እንዲታቀብ ቢጠይቅም ጥረቱ ሰሚ አለማግኘቱን ገልጿል።

ባለፈው በዚህ ዓመት አጋማሽ ላይ የኤርትራ መንግሥት የቀድሞ የሠራዊት አባላት ወደ የክፍሎቻቸው ለዳግም ሥልጠና እንዲመለሱ እና ሌሎች ዜጎቹ ከአገር ለመውጣት የሚጠበቅባቸውን መስፈርቶች ማጥበቁን ቢቢሲ መዘገቡ ይታወሳል።
በዚህም ከ60 ዓመት በታች የሆኑ በኤርትራ ሠራዊት ውስጥ ያገለገሉ ዜጎች ተመዝግብው ወደ ማሠልጠኛ እንዲገቡ፤ እንዲሁም ከ50 ዓመት በታች የሆኑ ሰዎች ደግሞ ተገቢውን ፈቃድ ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ሳያገኙ ከአገር እንዳይወጡ ዕገዳ መጣሉን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
በትግራይ ጦርነት አንድ ላይ ቆመው የትግራይ ኃይሎችን የወጉት የኤርትራ እና የኢትዮጵያ መንግሥታት ወዳጅነታቸው መቀዛቀዝ የጀመረው ጦርነቱን ያበቃው የፕሪቶሪያ ስምምነት ከተፈረመ በኋላ ነው።
በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ጉዳይ የኅልውና ጉዳይ መሆኑን በይፋ ካሳወቁ በኋላ የሁለቱ አገራት ግንኙነት ወደ ውዝግብ እና መካሰስ ተሸጋግሯል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ኤርትራ በውስጥ ጉዳያቸው ጣልቃ እየገባች ታጣቂዎችን እየደገፈች ነው የሚል ተደጋጋሚ ክስ ሲያቀርቡ የቆዩ ሲሆን፣ በቅርቡም የኤርትራ ኃይሎች ከያዟቸው የኢትዮጵያ ግዛቶች እንዲወጡ ተጠይቋል።
ከሁለቱም አገራት ከፍተኛ ባለሥልጣናት እና መገናኛ ብዙኃን በተደጋጋሚ የሚሰማው ንግግር ዳግም ጦርነት ሊፈነዳ ይችላል የሚል ስጋትን ፈጥሯል።
ኤርትራ ወታደራዊ ዝግጅት እያደረገች መሆኑን ያመለከተውን ሪፖርት ያወጣው 'ዘ ሴንትሪ' የተባለው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ዋነኛ ትኩረት የሚያደርገው ጦርነቶችን የሚደግፉ ስውር የገንዘብ ዝውውሮችን መከታተል ላይ ሲሆን፣ በአውሮፓውያኑ 2009 በኤርትራ ላይ የጦር መሳሪያ ማዕቀብ የተጣለባት ለሶማሊያ ጂሃዲስት ቡድኖች ድጋፍ ትደርጋለች በሚል ክስ መሆኑን ጠቅሷል።
ድርጅቱ በዚህ ሪፖርቱ ላይ ከሁለት ዓመት በፊት ባበቃው በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ውስጥ በተካሄደው ደም አፋሳሽ ጦርነት ወቅት የተፈጸሙ ሰቆቃዎችንም ጠቅሷል።
በትግራይ ኃይሎች እና በፌደራል መንግሥቱ መካከል በተካሄደው ጦርነት ወቅት የኤርትራ ሠራዊት የኢትዮጵያ መንግሥትን ደግፎ ተሳታፊ የነበረ ሲሆን፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸውን የአፍሪካ ኅብረት መረጃ ማመልከቱን ኤኤፍፒ ጠቅሷል።
የ'ዘ ሴንትሪ' ሪፖርት በጦርነቱ የተሳተፉ ሁሉም አካላት የጦር ወንጀሎችን መፈጸማቸውን በመጥቀስ፣ በተለይ በኤርትራ ሠራዊት የተፈጸሙት ግን "የታቀዱ እና የሚነጻጸሩ ይደሉም" ሲል ከስሷል።
