የዓመቱ የአገራት የሙስና ደረጃ ሪፖርት፤ ኢትዮጵያ በስንተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች?

Author

selam

Date Published

የዓመቱ የአገራት የሙስና ደረጃ ሪፖርት፤ ኢትዮጵያ በስንተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች?


በዓለም ላይ በሕዝባዊ አገልግሎቶች ዘርፍ ያለውን የሙስና ሁኔታ እየተከታተለ ዓመታዊ ሪፖርት የሚያወጣው ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል በተጠናቀቀው የአውሮፓውያኑ 2024 ዓመት የአገራትን የሙስና ደረጃን ይፋ አድርጓል።

ሪፖርቱ የ180 የዓለም አገራትን የሙስና ደረጃ ያወጣ ሲሆን ከፍተኛውን ነጥብ በማግኘት ሙስና በጣም በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኝባቸው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት እና ግጭት የሌለባቸው አገራት ሲሆኑ፣ ሙስና ሥር የሰደደባቸው ደግሞ ግጭት እና ቀውስ ያለባቸው አገራት መሆናቸውን አመልክቷል።

በአገራቱ ዝርዝሩ ውስጥ ያደጉ የሚባሉት አገራት ከፍተኛውን ነጥብ በማግኘት ዝቅተኛ ሙስና የተመዘገባባቸው በመሆን ከፊት ያሉትን ደረጃዎች ይዘዋል።

በአገራት ውስጥ ያለውን የሙስና ደረጃ ለመመዘን ከሚሰጠው ከፍተኛ የሙስና ነጥብ ከሆነው 100 ውስጥ 37 በማግኘት ኢትዮጵያ ከ180 አገራት 99ኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ሪፖርቱ አስፍሯል።

ይህ የአገራት የሙስና ሁኔታን አመላካች የሆነው ዝርዝር በዓለም አቀፍ ደረጃ በስፋት የሚጠቀስ ሲሆን፣ ባለሙያዎች እና የንግድ ሰዎች በዋናነት ከሙስና አንጻር የሚገመገሙት የአገራት ሕዝባዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ናቸው።

በዚህ ምዘናም በአገራት ውስጥ ያለው የሙስና ሁኔታን ዜሮ (በከፍተኛ ሁኔታ ሙስና የተንሰራፋበት) እስከ 100 (ሙስና አስከ ሌለበት) ድረስ ነጥብ በመስጠት ነው የአገራት ደረጃ የሚወሰነው።

በዓለም ዙሪያ የፀረ ሙስና እንቅስቃሴን በማራመድ በሚታወቅ በትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል አማካኝነት በየዓመቱ የሚወጣው ይህ የአገራት የሙስና ደረጃ ጠቋሚ ሪፖርት ውስጥ አብዛኞቹ የዓለም አገራት ተካተዋል።

ያለፈው ዓመትን በሸፈነው በዚህ ሪፖርት ኢትዮጵያ ከ180 አገራት በሕዝብ አገልግሎት ዘርፍ ባለ ሙስና 99ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠች ሲሆን፣ ይህም ቀደም ባለው የአውሮፓውያን ዓመትም በተመሳሳይ ደረጃ ላይ እንደነበረች ሪፖርቱ አመለክቷል።

በሪፖርቱ መሠረት ከሙስና አንጻር ከአጎራባች አገሮች አንጻር ኢትዮጵያ በተሻለ ደረጃ ላይ የምትገኝ ሲሆን፣ በዙሪያዋ ያሉ አገራት በሙሉ ከኢትዮጵያ ከፍ ባለሁኔታ ሙስና እንዳለባቸው ሪፖርቱ ይፋ አድርጓል።



በዚህም መሠረት ኬንያ 32 ነጥብ በማግኘት 121ኛ፣ ጂቡቲ በ31 ነጥብ 127ኛ፣ በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ የምትገኘው ሱዳን በ15 ነጥብ 170ኛ፣ ኤርትራ በ13 ነጥብ 173ኛ፣ ሶማሊያ በ9 ነጥብ 179ኛ እና ደቡብ ሱዳን በ8 ነጥብ 180ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

የአገራትን የሙስና ሁኔታን በሚያሳየው ደረጃ ላይ ከሚሰጠው 100 አጠቃላይ ነጥብ ከግማሽ በላይ የሚያስመዘግቡ አገራት በጥሩ ሁኔታ ላይ ያሉ የሚባሉ ናቸው።

ከዚህ አንጻር በአጠቃላይ በአፍሪካ በተሻለ ደረጃ ላይ የሚገኙት አገራት ሲሸልስ (በ72 ነጥብ 18ኛ)፣ ኬፕ ቬርዲ (በ62 ነጥብ 35ኛ) ቦትስዋና (በ57 ነጥብ 43ኛ) እና ሞሪሺየስ (በ51 ነጥብ 56ኛ) ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

በምዘናው ውስጥ ከተካተቱት 180 አገራት መካከል ሙስና በጣም በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝባቸው ቀዳሚ አስር አገራት የአውሮፓው እና የእስካንዴኔቪያን አገራት ናቸው።

በዚህ መመዘኛ 100 ከመቶ በማግኘት ፍጹም ከሙስና የጸዳ አገር ባይኖርም ለተከታታይ ዓመታት በአንደኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ዴንማርክ አሁንም በ90 ነጥብ ትመራለች፣ ፊንላንድ በ88 ነጥብ ሁለተኛ እና ሴንጋፖር በ84 ነጥብ በሦስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።