ዩኬ እና አሜሪካ አለም አቀፉን የሰው ሰራሽ አስተውሎት ስምምነት ለመፈረም አሻፈረኝ አሉ
Author
selam
Date Published
ዩኬ እና አሜሪካ አለም አቀፉን የሰው ሰራሽ አስተውሎት ስምምነት ለመፈረም አሻፈረኝ አሉ

ዩናይትድ ኪንግደም እና አሜሪካ አለም አቀፉን የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (ሰው ሰራሽ አስተውሎት) ስምምነት አንፈርምም አሉ።
አገራቱ ይህንን አቋማቸውን ያስታወቁት በቅርቡ በፓሪስ በኤአይ ላይ በተካሄደ አለም አቀፍ ጉባኤ ላይ ነው።
ፈረንሳይ፣ ቻይና እና ህንድን ጨምሮ በርካታ አገራት በዚህ ጉባኤ ላይ የተደረሰውን ይህንን ስምምነት የፈረሙ ሲሆን ይህም የቴክኖሎጂው እድገት "ክፍት"፣ "አካታች" እና "ሥነ ምግባራዊነትን" የተከተለ ለመሆኑ ለማረጋገጥ ያለመ ነው ተብሏል።
የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት የብሔራዊ ደህንነት እና አለም አቀፍ አስተዳደርን በተመለከተ ስጋት ስላደረበት በመመሪያው ላይ ፊርማ ማኖር አልቻልንም ሲሉ ባለስልጣናቱ አጭር መግለጫ ሰጥተዋል።
ቀደም ሲል የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ጄዲ ቫንስ በፓሪስ ለተገኙ ልዑካን እንደተናገሩት ከልክ ያለፈ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (ኤአይ) ቁጥጥር "በለውጥ እየተመነደገ ያለውን ኢንዱስትሪ ሊገድለው ይችላል" ብለዋል።
ቫንስ ለአለም መሪዎች በአስተላፉት መልዕክት አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ለ "ትራምፕ አስተዳደር መልካም እድል በመሆኑ አያባክነውም" ካሉ በኋላ ከደህንነት ይልቅ "የኤአይ የእድገት ፖሊሲዎች" ቅድሚያ ሊሰጣቸው እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የምክትል ፕሬዚዳንቱ አስተያየት ተጨማሪ የቁጥጥር አስፈላጊነትን ከሚሟገቱት ከፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን አስተያየት ጋር የሚጋጭ ይመስላል።
ማክሮን በጉባዔው ላይ "አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ወደፊት እንዲራመድ እነዚህ ህጎች አስፈላጊ ናቸው" ሲሉ ተናግረዋል።
Open for Advertising
ዩናይትድ ኪንግደም ቀደም ሲል የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ደህንነትን በመግፋት ቀዳሚ አገር የነበረች ሲሆን የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ በአውሮፓውያኑ 2023 የመጀመሪያውን የኤአይ የደህንነት ጉባኤን አካሂደው ነበር።
መረጃዎችን የሚያጣራው ፉል ፋክት የተሰኘው ድርጅት የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኃላፊ የሆኑት አንድሪው ደድፊልድ የዩኬ መንግሥት የፓሪስን ስምምነት ላለመፈረም የደረሰበት ውሳኔው አደጋ ላይ ጥሎታል ብለዋል።
"የዩናይትድ ኪንግደም አለም አቀፉን የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ስምምነት ላለመፈረም የደረሰበት ውሳኔ ደህንነቱን የጠበቀ፣ ስነ ምግባር የተከለ እንዲሁም ተዓማኒነት ያለው የኤአይን ፈጠራ በማምጣት ደረጃ ሲከተለው የነበረውን የዓለም መሪነቱን ስፍራ ያሳጣዋል"ሲሉም አክለዋል።
በመላው ዩኬ በኤአይ ዘርፍ ውስጥ የተሰማሩ ድርጅቶችን የሚወክለው ዩኬኤአይ የተተሰኘው የንግድ ተቋም በበኩሉ ትክክለኛ ውሳኔ ነው ብሏል።
በ60 አገራት የተፈረመው ይሄ ስምምነት የኤአይ ተደራሽነትን በማሳደግ እንዲሁም የቴክኖሎጂው ዕድገት ግልጽነት የተሞላው፣ አስተማማኝ እና ደህንነቱ የተጠበቀ በማድረግ የዲጂታል መከፋፈል ለመቀነስ ያለመ ነው።
"አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን ለአለማችን ህዝቦች እንዲሁም ለፕላኔቷ ዘላቂ እንዲሆን" የሚል ቀዳሚ አላማን አንግቧል።
የኤአይ የኃይል (ኤነርጂ) አጠቃቀም ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህ ጉባዔ ላይ ተነስቷል። የኤአይ ኃይል አጠቃቀም ትናንሽ አገራት የሚጠቀሙትን ያህል ኃይል ሊስተካከል እንደሚችል ባለሙያዎች እያስጠነቀቁ ይገኛሉ።