“በተራራና በጅረት የነበረውን ወታደራዊ ስልጠና አሁን ላይ ወደ ባሕር ቀይረነዋል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
Author
amc-admin
Date Published

“በተራራና በጅረት የነበረውን ወታደራዊ ስልጠና አሁን ላይ ወደ ባሕር ቀይረነዋል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አሰለፍ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን (የካቲት 15 ቀን 2018 ዓ.ም.)፡ - በባሕር ላይ የሚፈጸሙ ወታደራዊ ተልዕኮዎች በኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ሥልጠና ውስጥ መካተት መጀመራቸውን የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታወቁ፡፡
የመከላከያ ሠራዊት የልዩ ዘመቻዎች እዝ 65ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ዛሬ በሐዋሳ በድምቀት ተከብሯል፡፡
በሥነ - ስረዓቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) “በምድር፣ በተራራና በጅረት ይሰጥ የነበረውን ወታደራዊ ስልጠና አሁን ላይ ወደ ባሕር ቀይረነዋል፡፡” ብለዋል፡፡
በታላቁ ሕዳሴ ግድብ እና በወንዝ ዳርቻ መሰል ልማት ሥራዎች ሳቢያ ከውሃ የመራቅ፣ ከውሃ የመሸሽ እና እንደ ባዕድ አምልኮ የማየት ክፉ ልማድ አሁን መቀየሩን አመልክተዋል፡፡
ስልጡን ሠራዊት የምንገነባው ውጊያና ሽብር እንዳይፈጠር፤ ከተፈጠረም በአጭር ጊዜ ለመቋጨት ነው፤ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የልዩ ዘመቻዎች እዝ ቀይ ቦኔት ለባሾቹ ውጊያ የሚጨርሱ እና ውጊያ የሚያስቀሩ ናቸው ብለዋል፡፡
የእኛ ዝግጅት በአፍሪካ ሰላምና ብልጽግና ለማረጋገጥ እንዲሁም በቀጣናው ላሉ አገራት አለኝታና መከታ ለመሆን ነው፡፡ ወንድም ሕዝቦችን ደግፈን ሽብርን ለመከላከል እና ልማት እና ብልጽግናን በቀጣናው ለማረጋገጥ የላቀ አቅም ያለው ስልጡን ሠራዊት (ኤሊት ፎርስ) ገንብተናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የዘመኑን ቴክኖሎጂ የሚጠቀም፣ በምሽግ ብቻ ሳይሆን በስተራቴጂክ ግንባሮች ውጊያን ድል የሚያደርግ እና የሚያሳጥር ሠራዊት ኢትዮጵያ ስለገነባች አፍሪካውያን እንኳን ደስ አላችሁ ሲሉም ገልጸዋል፡፡

