የስፔን ፖሊስ ቅንጡ ሆቴሎችን በአንድ ሳንቲም የተከራየውን የሳይበር ጠላፊ በቁጥጥር አዋለ
Author
amc-admin
Date Published

የስፔን ፖሊስ ቅንጡ ሆቴሎችን በአንድ ሳንቲም የተከራየውን የሳይበር ጠላፊ በቁጥጥር አዋለ
**********************
አሰለፍ ሚዲያ (የካቲት 13 ቀን 2018 ዓ.ም.)፡ - የስፔን ፖሊስ የሆቴል ክፍሎችን መያዣ ድረ-ገጽን በመጥለፍ የቅንጦት ክፍሎችን በአንድ ሳንቲም ብቻ የተከራየውን የ20 ዓመት ወጣት በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቋል።
ድርጊቱ በዓይነቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የታወቀ የሳይበር ወንጀል መሆኑ ተገልጿል፡፡
ተጠርጣሪው በድረ-ገጹ የክፍያ ስርዓት ሰርጎ በመግባት የኤሌክትሮኒክ ክፍያ ስርዓትን በማዛባት፣ በመቀየር እና ሂደቱን በማረጋገጥ የሆቴሎቹን ቅንጡ ክፍሎች እንደተከራያቸው ይታመናል፡፡
የፖሊስ መረጃ እንደጠቆመው ቅንጡ ክፍሎቹ ለአንድ ምሽት ከ1000 እስከ 1200 ዩሮ ዋጋ ያላቸው ሲሆን፤ ይሁን እንጂ የሳይበር ወንጀለኛው አንድ ሳንቲም ብቻ ከፍሎባቸው የማጭበርበር ወንጀሉን ፈጽሟል፡፡
የስፔን ብሄራዊ ፖሊስ “ይህ የሳይበር ጥቃት በተለይ የክፍያ ማረጋገጫ ሥርዓትን ለመለወጥ የተነደፈ ሲሆን ይህንን ዘዴ የተጠቀመ ወንጀል ስናገኝ ይህ የመጀመሪያው ነው” ብሏል።
ፖሊስ እንዳለው የስፔን ዜጋ የሆነው ይህ የ20 ዓመት ወጣት በቅንጡ ሆቴሎቹ ውስጥ በነበረው ቆይታ በክፍሎቹ ሚኒባር ውስጥ የተቀመጡ ምግቦችን ይበላ የነበረ ሲሆን አልፎ አልፎም ሂሳቦችን ሳይከፍል ይወጣ እንደነበር ተገልጿል።
ወንጀለኛው በቁጥጥር ስር በዋለበት ጊዜም በማድሪድ ሌግዠሪ ሆቴል ውስጥ አርፎ የነበረ ሲሆን፤ በድምሩ ለአራት ሌሊቶች 4,000 ዩሮ የተጭበረበረ ክፍያ ፈጽሟል፡፡
ግለሰቡ በሆቴሉ ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት ባረፈበት ወቅት ከ20,000 ዩሮ በላይ ኪሳራ አስከትሏል ሲል የፖሊስ ቃል አቀባይ ተናግሯል።

