ግብፅ እና ኬንያ የአባይን ወንዝ ለመጠበቅ በጋራ ትብብር እንደሚሰሩ አስታወቁ
Author
amc-admin
Date Published

ግብፅ እና ኬንያ የአባይን ወንዝ ለመጠበቅ በጋራ ትብብር እንደሚሰሩ አስታወቁ
አሰለፍ ሚዲያ (የካቲት 10 ቀን 2018 ዓ.ም.)፡ -ግብፅ እና ኬንያ በናይል ተፋሰስ ጉዳዮች ላይ የበለጠ ትብብር ለማድረግ ቃል መግባታቸውን የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ትናንት ገልጿል።
አህራም ኦንላይን እንደዘገበው የግብፁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብዴላቲ እና የውሃ ሃብት ሚኒስትር ሃኒ ሰዊላም ከኬንያ አቻዎቻቸው ሙሳሊያ ሙዳቫዲ እና ኤሪክ ሙሪቲ ጋር በናይሮቢ መክረዋል፡፡
በናይሮቢ በሰጡት የጋራ መግለጫ፤ በናይል ተፋሰስ ኢኒሼቲቭ የምክክር ሂደት የሁሉንም የተፋሰስ ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ መልኩ ትብብር፣ አካታችነት እና ውይይት ለማጠናከር ተስማምተዋል።
የሚንስትሮቹ ውይይት ከዓለም አቀፍ ህግጋት ጋር በተጣጣመ መልኩ የውሃ ደህንነትን፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትን እና የስርዓተ-ምህዳር ጥበቃን ለማስፋፋት የሚደረጉ ሰፊ ጥረቶች አካል መሆኑ ተጠቁማል።
ሚኒስትሮቹ በአባይ ተፋሰስ ጉዳዮች ላይ የሚያደርጉትን ምክክር አጠናክሮ ለመቀጠልና በተፋሰስ ሀገራት መካከል ያለውን ቀጠናዊ ውህደት ለማጠናከር ተስማምተዋል።
ከውሃ ትብብር ባሻገር በአፍሪካ ቀንድ፣ በቀይ ባህር እና በታላላቅ ሀይቆች አካባቢ ያሉ አህጉራዊ ለውጦች እንደዚሁም በሶማሊያ እና በሱዳን መረጋጋትን ወደ ነበረበት ለመመለስ የሚደረገውን ጥረት የተመለከቱ ጉዳዮች በሚንስትሮቹ ውይይት ወቅት መነሳታቸውን ዘገባው ጠቁሟል፡፡
