በአምስት ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ የነዳጅ ዋጋ ምን ያህል ጨመረ?

Author

selam

Date Published

በአምስት ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ የነዳጅ ዋጋ ምን ያህል ጨመረ?

ባለፉት አምስት ዓመታት የነዳጅ ዋጋ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል። መንግሥት በየወሩ መጀመሪያ ላይ በአገሪቱ የሚኖረውን የነዳጅ መሸጫ ዋጋን ይፋ ያደርጋል።

ይህ ተመንም አንዳንድ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ ጭማሪ ሲያሳይ ሌላ ጊዜ ደግሞ ባለበት ሲቀጥል የቆየ ሲሆን፣ ነገር ግን አስካሁን የመቀነስ ሁኔታን ሲያሳይ አልታየም። ለዚህም የተለያዩ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ።

አሁንም በጥር ወር የነበረው የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ በየካቲት ወር በነበረበት እንደሚቀጥል የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

ባለፉት ዓመታት በአገሪቱ የታየው የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ከፍተኛ መሆኑ፣ በሁሉም ምርት እና አገልግሎቶች ላይ ተንጸባርቋል።

* * *

ጥቂት ወደኋላ መለስ ብንል ከአምስት ዓመት በፊት በኢትዮጵያ ውስጥ 100 ብር 4 ሊትር ቤንዚን ይገዛ ነበር፤ እንዲያውም መለስ ነበረው።

ያኔ በ100 ብር 5 ሊትር ናፋጣ አሊያም ነጭ ጋዝ ተሸምቷል።

ዛሬ 100 ብር መግዛት የሚችለው አንድ ሊትር ናፍጣ ወይም ነጭ ጋዝን ብቻ ነው። አንድ ሊትር ቤንዚን ለመግዛት ከ100 ብር በላይ ያስፈልጋል።

በዚህ ስሌት የነዳጅ ዋጋ በአምስት ዓመታት ውስጥ ከ360 በመቶ በላይ አሻቅቧል።

በእነዚህ ዓመታት በዓለም ዙሪያ የነዳጅ ዋጋ ላይ ቀጥተኛ ተጽእኖ ያሳረፉ ለውጦች ተከስተዋል።

ለአብነት፣ በዓለም የነዳጅ ገበያ 11 በመቶ ድርሻ ያላት ሩሲያ ከዩክሬን ጋር ጦርነት ውስጥ ገብታለች።

የዓለምን የድፍድፍ ነዳጅ አቅርቦትን 40 በመቶ ድርሻ የሚይዙት የ'ኦፔክ ፕላስ' የነዳጅ ላኪ ሀገራት ኅብረት ምርታቸውን በሁለት በመቶ ቀንሰዋል።

ሆኖም እነዚህ ሁሉ ምክንያቶች በዓለም ዙሪያ የነዳጅ ዋጋ ላይ ያስከተሉት "መጠነኛ" የዋጋ ለውጥ ነው።

ታዲያ በኢትዮጵያ የነዳጅ ዋጋ ይህንን ያህል ለምን ጨመረ?

ከዚያ በፊት ይህንን ጥያቄ እንመልስ።

ለመሆኑ ባለፉት አምስት ዓመታት የነዳጅ ምርቶች ዋጋ ከየት ተነስቶ የት ደረሰ?


በኢትዮጵያ የነዳጅ ዋጋ ከ2013 – 2017


በኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመት የነበረው የነዳጅ ምርቶች ዋጋ ተደጋጋሚ ለውጥ የተደረገበት ነው።

2013

ከአምስት ዓመት በፊት ጥቅምት 1/2013 ዓ.ም. የቀድሞው የንግድ እና ኢንደስትሪ ሚኒስቴር በነዳጅ ዋጋ ላይ ጭማሪ መደረጉን አስታውቆ ነበር።

በወቅቱ 1 ሊትር ቤንዚን 21 ብር ከ87 ሳንቲም፣ ናፍጣ እና ነጭ ጋዝ ደግሞ 19 ብር ከ9 ሳንቲም እንዲሸጥ ተወስኗል።

በተመሳሳይ ዓመት የካቲት መጨረሻ ላይ ይኸው መሥሪያ ቤት ሌላ የዋጋ ለውጥ አድርጎ ቤንዚን በሊትር ከጥቅም ወር ዋጋው በ3 ብር ከ 99 ሳንቲም ወይም በ18 በመቶ በመጨመር 25 ብር ከ86 ሳንቲም ሆኗል።

የአንድ ሊትር ናፍጣ እና ነጭ ጋዝ ዋጋ ደግሞ ወደ 19 ብር ከ9 ሳንቲም ከፍ ብሏል። የ3 ብር ከ28 ሳንቲም ወይም የ16 በመቶ ጭማሪ ማለት ነው።

2014

ስያሜውን ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ወደሚል የተቀየረው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት በ2014 ኅዳር ወር ላይ ባደረገው ለውጥ የአንድ ሊትር የቤንዚን ዋጋ ቀድሞ ከነበረው ዓመት የ5 ብር ከ88 ሳንቲም ወይም የ22 በመቶ ጭማሪ አድርጓል። በዚህም አንድ ሊትር ቤንዚን ወደ 31 ብር ከ74 ሳንቲም አሻቅቧል።

ናፍጣ እና ነጭ ጋዝ እያንዳንዳቸው በሊትር ወደ 28 ብር ከ94 ሳንቲም ከፍ ብለው የ5 ብር ከ 76 ሳንቲም (24 በመቶ) ጭማሪ አሳይተዋል።

በ2014 ሰኔ ወር ሚኒስቴሩ ሌላ ጭማሪ አደርጓል።

ይህ ወቅት የኢትዮጵያ መንግሥት ለነዳጅ ምርቶች ሲያደርግ የነበረውን ድጎማ መቀነስ የጀመረበት ነው።

በዚህም ሳቢያ በነዳጅ ምርቶች ላይ እስከ 50 በመቶ የዋጋ ጭማሪ ታይቷል።

ቤንዚን በሊትር የ16 ብር ጭማሪ ተደርጎበት 47 ብር ከ83 ሳንቲም የመሸጫ ዋጋ ተቆርጦለት ነበር።

ይህም በዚያው ዓመት ኅዳር ወር ላይ ሲሸጥበት ከነበረበት የ50 በመቶ ጭማሪ የታየበት ነው።

ቀደም ካለው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ደግሞ የ118 በመቶ ወይም የ25 ብር ከ96 ሳንቲም ጭማሪ ማለት ነው።

በሌላ አገላለጽ ከአንድ ዓመት በፊት (በ2013) ሁለት ሊትር ቤንዚን መግዛት የሚችል ገንዘብ በዚያ ዓመት (2014) አንድ ሊትር ከመግዛት አይዘልም ነበር።

በነጭ ጋዝ እና በናፍጣ ላይ የታየው ጭማሪ ከቤንዚንም ከፍ ያለ ነው።

በዚያው ዓመት ከነበሩበት ዋጋ 55 በመቶ ወይም የ17 ብር 55 ሳንቲም ጭማሪ ታይቶባቸዋል።

ከ2013 አንጻር ሲታዩ ደግሞ በ29 ብር ከ12 ሳንቲም ወይም በ146 በመቶ አሻቅበዋል።



2015

በ2015 ዓ.ም. ሚኒስቴሩ በታኅሣሥ እና በነሐሴ መጨረሻ ላይ የዋጋ ጭማሪ መደረጉን አስታውቆ ነበር።

በታኅሣሥ ወር ቤንዚን በሊትር 61 ብር ከ29 ሳንቲም እንዲሸጥ ተወስኖ የነበረ ሲሆን፣ ነሐሴ ላይ በ13 ብር 56 ሳንቲም (በ22 በመቶ) ጨምሮ 74 ብር ከ85 ሳንቲም እንዲሸጥ ተወስኗል።

በዚያው ዓመት ታኅሣሥ ላይ ናፍጣ እና ነጭ ጋዝ በሊትር ከነበሩበት 67 ብር ከ30 ሳንቲም ወደ 76 ብር ከ34 ሳንቲም አሻቅበዋል።

ይህም የ9 ብር ከ04 ሳንቲም ወይም የ13 በመቶ ጭማሪ የታየበት ነበር።

2016

በ2016 ጥቅምት ወር ቤንዚን በሊትር 77 ብር ከ65 ሳንቲም እንዲሁም ናፍጣ እና ነጭ ጋዝ 79 ብር ከ76 ሳንቲም እንዲሸጥ መወሰኑን ሚኒቴሩ አስታውቋል።

በዚያው ዓመት መጨረሻ ወር ሌላ ጭማሪ ተደርጓል። በነሐሴ በተደረገው ጭማሪ የአንድ ሊትር ቤንዚን ዋጋ በ6 በመቶ (በ4 ብር ከ95 ሳንቲም) የጨመረ ሲሆን፣ ነጭ ጋዝ እና ናፍጣ በ9 በመቶ (በ6 ብር ከ99 ሳንቲም) ጨምሯል።

በዚህም የአንድ ሊትር ቤንዚን ዋጋ 82 ብር ከ 60 ሳንቲም፤ የነጭ ጋዝ እና የናፍጣ የአንድ ሊትር ዋጋ ደግሞ 83 ብር ከ74 ሳንቲም ሆኗል።

ይህ ጭማሪ ከመደረጉ አንድ ወር ቀድሞ የኢትዮጵያ መንግሥት የውጭ ምንዛሬ ዋጋ በገበያ እንዲመራ መወሰኑን ይፋ አድርጓል።




የነዳጅ ዋጋ ለምን ጨመረ?

የውጭ ምንዛሪ ለውጥ እና የነዳጅ ድጎማ መቀነስ ለዋጋው መጨመር ዋነኛ ምክንያቶች እንደሆኑ በዩናትድ ኪንግድም የሚገኙት የምጣኔ ሀብት ባለሙያ አብዱልመናን መሐመድ (ዶ/ር) ይናገራሉ።

የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት በተቀሰቀሰበት ወቅት የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ታይቶበታል።

"ከዚያ በኋላ ግን ብዙም የዋጋ መለዋወጥ አልመጣም። ስለዚህ [በኢትዮጵያ የነዳጅ ዋጋ የጨመረበት] መሠረታዊ ምክንያቱ የውጭ ምንዛሪ ለውጥ ነው" ይላሉ።

ሌላኛው ምክንያት ደግሞ መንግሥት ለነዳጅ ሲያደረግ የነበረው ድጎማ መነሳት ነው።

የኢትዮጵያ መንግሥት "በጥቂት ዓመታት" ውስጥ ነዳጅን ለመደጎም ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከሦስት ዓመት በፊት በተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ ተናግረው ነበር።

ይህ ድጎማ ዓላማውን እየሳተ እንደሆነ በመግለጽም "ሥርዓት እንደሚበጅለት" አንስተዋል።

ከዚያም በኋላ መንግሥት የነዳጅ ድጎማን ቀስ በቀስ ማንሳት በመጀመሩ የነዳጅ ዋጋ እየጨመረ ይገኛል።

አብዱልመናን (ዶ/ር) የድጎማው መነሳት መንግሥትን ከከፍተኛ ወጪ እንደሚያድነው ይናገራሉ።

በተቃራኒው ጫናው በቀጥታ ወደ ዜጎች ይወርዳል። ሸማቾች የነዳጅ ዋጋን ሙሉ በሙሉ እንዲሸፍኑ ያደርጋል።

በዚህ ሂደት "ዜጎች ይጎዳሉ ምንም ጥርጥር የለውም" የሚሉት ባለሙያው "ኢኮኖሚያቸው የጠነከረ፣ ገቢያቸው ጥሩ የሆነ ዜጎች ያሉበት ሀገር ላይ የደጎማ መነሳትን መቋቋም ይችላሉ። እኛ ጋር ኢኮኖሚው ተቀዛቅዟል፣ የግጭቶች ጉዳይ አለ፣ የዋጋ ግሽበቱ በጣም ትልቅ ነው። በዚያ ሁኔታ መንግሥት የሚያደርገውን ድጋፍ ሲያነሳ ነገሩን በጣም ከባድ ያደርገዋል" ሲሉ አክለዋል።

ስለዚህ የነዳጅ ድጎማው እየተነሳ ያለበት ጊዜ ትክልል እንዳልሆነ ያምናሉ።

ሌላው እንደ አይኤምኤፍ እና የዓለም ባንክ ያሉ ተቋማት የመንግሥት ድጎማን እንደማይደግፉ ባለሙያው ያነሳሉ።

"እንደ ሴፍቲኔት ያሉ ለድሆች የሚሰጥ ካልሆነ በስተቀር ኤሌክትሪክ ወይም ነዳጅ ላይ የሚደረግ ድጎማን በፍጹም አይደግፉትም። ማንም ሰው ባቅሙ ይግዛ የሚሉ ናቸው" ሲሉ ያስረዳሉ።

ከዚህ ሁሉ በላይ ትልቁ ጥያቄ ያለው የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ነው።

ትልቁ ጥያቄ "ብራችን በዚህ ደረጃ እንዴት ወደቀ [የሚለው] ነው? ብራችን በዚህ ደረጃ ባይወደቅ ኖሮ ነዳጅም በዚህ ደረጃ ውድ አይሆንም ነበር። ለብር መውደቅ ዋነኛ ምክንያቱ ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት በገፍ ያተመው ብር ነው ይኼን ሁሉ ችግር ይዞ የመጣው" ይላሉ።

Related Posts

ዩናይትድ ኪንግደም እና አሜሪካ አለም አቀፉን የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (ሰው ሰራሽ አስተውሎት) ስምምነት አንፈርምም አሉ። ፈረንሳይ፣ ቻይና እና ህንድን ጨምሮ በርካታ አገራት በዚህ ጉባኤ ላይ የተደረሰውን ይህንን ስምምነት የፈረሙ ሲሆን