ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ የህወሓት አመራር "ሰፊ ወታደራዊ ዝግጅት" እያደረገ ነው አሉ
Author
amc-admin
Date Published

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ የህወሓት አመራር "ሰፊ ወታደራዊ ዝግጅት" እያደረገ ነው አሉ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፤ የህወሓት አመራር "ሰፊ ወታደራዊ ዝግጅት"፣ "የጦር መሣሪያ ግዥ" እና "ወታደራዊ ቅስቀሳዎችን እያደረገ ነው" ሲሉ በትግርኛ በሰጡት ቃለ መጠይቅ ከሰሱ።
በፌደራል መንግሥት በኩል "በጭራሽ ትግራይ ላይ የሚጀመር ጦርነት እንደሌለ" አረጋግጣለሁ ሲሉም ተናግረዋል።
ትናንት ማክሰኞ የካቲት 24/2018 ዓ. ም. ምሽት ላይ የተላለፈው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ቃለ መጠይቅ በአብዛኛው ያተኮረው ከትግራይ ክልል እና ከኤርትራ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ነው።
ዐቢይ፤ ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር ከነበራቸው የ40 ደቂቃ ገደማ ቆይታ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ጊዜ የወሰደው ስለ ትግራይ ጦርነት እና ስለ ፕሪቶሪያ ስምምነት ለተነሱ ጥያቄዎች የተሰጠው ምላሽ ነው።
የፌደራል መንግሥት በፕሪቶሪያው ስምምነት የተጣሉበትን ግዴታዎች "እንደፈጸመ" የገለጹት ዐቢይ፤ "አሁን ችግር ሆኖ ያለው ከወልቃይት አካባቢ የተፈናቀሉትን [ነዋሪዎች] የሚመለከት ነው" ብለዋል።
"ይህ ደግሞ ግትር አቋም ባለው ቆሞ ቀሩ ኃይል ምክንያት አልተሳካም" ሲሉ በህወሓት ውስጥ ይገኛል ያሉትን ቡድን ተጠያቂ አድርገዋል። "ብዙ ጊዜ ተነጋግረናል አሁንም እምነታችን ምን እንደሆነ ሕዝባችን ያውቀዋል። ነገር ግን በቆሞ ቀሩ ግትር አቋም ምክንያት ያሰብነው ሊሳካ አልቻለም" ሲሉም ተናግረዋል።
በፕሪቶሪያው ስምምነት ውስጥ "ትልቁ የቤት ሥራ" ብለው የሚወስዱት "ከወልቃይት የተፈናቀሉ" ነዋሪዎችን ጉዳይ እንደሆነ ያነሱት ዐቢይ፤ "ተፈናቃዮች የግድ ወደ ቦታቸው መመለስ አለባቸው" ሲሉ ተደምጠዋል።
የሁለት ዓመቱን ጦርነት ያስቆመው የፕሪቶሪያ ስምምነት "በሙሉነት እንዳይፈጸም" ምክንያት ከሆኑ አንዱ "ህወሓት ሕገ መንግሥቱንና ተቋማትን ባለማክበር ወደ ጎን" መተዉ እንደሆነም በማንሳት ወቅሰዋል። "የብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ሕግ አልተቀበለም" ሲሉም ላቀረቡት ክስ ማሳያ ጠቅሰዋል።
"ሁሉም ወገኖች" ተግባራቸውን ካከናወኑ "አብዛኛው ችግር ይፈታል" የሚል ዕምነት እንዳላቸው የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ነገር ግን የህወሓት አመራሮች "ለጦርነት እየተዘጋጁ ነው" ሲሉ ከስሰዋል። "ቆሞ ቀሩ ቡድን በሰፊው ወታደራዊ ዝግጅት ላይ ይገኛል። በጣም የሚገርመው ደግሞ በግልጽ ፀረ ኢትዮጵያ ከሆኑ ኃይሎች ጋር መሰለፉ ነው" ብለዋል።
እንደ ዐቢይ ገለጻ፤ ቡድኑ "ተስፋውን ወደ ውጭ ኃይሎች" ያደረገው "በአባላቱ ላይና በሕዝቡ ላይ የነበረው ተስፋ እየተዳከመ" በመምጣቱ ነው። "የትግራይ ሕዝብ በተለይ ወጣቱ፣ ታጣቂዎችንም ጨምሮ እምቢ ለጦርነት ሲል እያየን ነው" በማለት ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ ቡድኑ፤ "ባለችው አቅም ወታደራዊ ቅስቀሳዎችን እያደረገ ነው" ያሉት ዐቢይ፤ "የትግራይ ወርቅ እና ሌሎች ማዕድናትን እየበዘበዘ ለጦር መሣሪያ ግዥ እያዋለው ነው" ሲሉ ወንጅለዋል።
ዐቢይ፤ ህወሓት "የጦርነት ቅስቀሳውን" እያከናወነ ያለው "ከምርጫ ቦርድ ተሰረዝኩ፣ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው አልተመለሱም" የሚል ምክንያቶች በመጥቀስ እንደሆነ ተናግረዋል። እነዚህ ችግሮችንም "ራሱ የፈጠራቸው" ሲሉ ጠርተዋል።
"የእኔ አቋም ከቃላት አልፎ ወደ ወታደራዊ ትንኮሳ ከገባ ግን 'እንደ ቀድሞ መስሎሽ ጎርፉ ይወስድሻል' ብቻ ነው ማለት የምችለው" ሲሉም አስጠንቅቀዋል።
አክለውም፤ "በበኩላችን በፍጹም በጭራሽ ትግራይ ላይ የሚጀመር ጦርነት እንደሌለ ለማረጋገጥ እና ለመግለጽ እወዳለሁ። በትግራይ ዳግም ውጊያ የመጀመር ፍላጎት እና ሐሳብ እንደሌለን ሕዝባችን ማወቅ አለበት" ሲሉ ተናግረዋል።
