የምታጌጥበትን ወርቅ ሸጣ የኦቲዝም ማዕከል የከፈተችው እናት

Author

selam

Date Published

የምታጌጥበትን ወርቅ ሸጣ የኦቲዝም ማዕከል የከፈተችው እናት


ታዳጊው በሰንሰለት ታስሮ ያየችው በአንድ አጋጣሚ ነበር። ወላጆቹ በእርሱ ምክንያት ተለያይተዋል። እናት ልጇን የምታስድግበት ምንም ዓይነት ገቢ የላትም። ልጇን አጠገቧ በሰንሰለት እያሰረች የቀን ሥራ በመሥራት ነበር የምትተዳደረው።

ይህ የሁለት ልጆች እናት ለሆነችው ኢማን ልብን የሚነካ አጋጣሚ ነበር።

"በሰንሰለት ሲታሰር የማውቀው ውሻ ነው" የምትለው ኢማን፣ መናገር የማይችለው ታዳጊ በዚህ ሁኔታ ታስሮ ማየቷ የሕይወቷን አቅጣጫ እንደለወጠው ትናገራለች።

"በልጁም፣ በእናቱም ቦታ ሆኜ ያሉበትን ሁኔታ አሰብኩት። ከአእምሮዬ በላይ ሆነብኝ" ትላለች።

በዚህም ምክንያት ለሦስት ወራት ያህል ምግብ መመገብ እና መረጋጋት ተስኗት እንደነበር ታስታውሳለች።

ኢማን ቤተሰብ ለመጠየቅ ነበር ከሁለት ልጆቿ ጋር በአማራ ክልል ወደ ምትገኘው ደሴ ከተማ ያቀናችው። ከሙሉ ቤተሰቧ ጋር ወደ ካናዳ ለመሄድም ሂደቶችን ጀምራ ነበር።


ኢማን መሐመድ የተወለደችው በደሴ ከተማ ሲሆን፣ እድገቷ በአዲስ አበባ ነው። ከዚያ ግን አክስቶቿ ወዳሉበት ሳዑዲ አረቢያ በመሄድ አብዛኛውን ዕድሜዋን በዚያ አሳልፋለች።

ትዳር መሥስርታ ሁለት ልጆችን ያፈራችውም እዚያው ሳዑዲ ውስጥ ነው።

ኢማን እንደምትለው የመጀመሪያ ልጇ እስከ አምስት ዓመቷ ድረስ መናገር አትችልም ነበር። ሰዎችን ስታማክርም 'ከልጆች ጋር አገናኛት' የሚል ምክር ነበር የምታገኘው። በልጃቸው ላይ ያዩት ሌላ አካላዊ ምልክት ስላልነበረም በጊዜ ሒደት ይስተካከላል የሚል ተስፋ ነበራት።

"ልጆቼን ይዤ ወጥቼ የማዝናናት ልማድ ነው ያለኝ" የምትለው ኢማን፤ የተባለችውን ብታደርግም በልጇ ላይ ለውጥ ማየት እንዳልቻለች ትናገራለች።

ልጇ ኦቲዝም እንዳለባት ያወቀችው ቤተሰብ ለመጠየቅ ወደ ኢትዮጵያ በሄደችበት አጋጣሚ ነበር።

"ሲነገረኝ ማመን አልቻልኩም ነበር፤ ሆኖም በልጄ ላይ ለመሥራት በሐኪሙ ፊት ቃል ገባሁ" ትላለች።

ልጇን ለመርዳት ስለኦቲዝም ማንበብ እና መጠየቅ ብትጀምርም ሆድ ይብሳት እንደነበር ግን አልሸሸገችም፤ ዓይኖቿም ለእንባ ቅርብ ነበሩ። ፈጣሪዋን የምታማርርበት ጊዜም ብዙ ነበር።

ታዲያ በዚህ በተደበላለቀ ስሜት ውስጥ ሳለች ነበር 'ዱዓ' እንድታደርግላት የነገረቻት ሴት "የባሰ አለ" ስትል ወደ ታዳጊው እናት የወሰደቻት።

የታዳጊው ሁኔታ በጣም የሚያሳዝን ነበር። በህመሙ ላይ የኑሮ ሁኔታው ተደራርቦበት ከሰው ተራ ወጥቶ ነበር የተመለከተችው። እናቱም ብትሆን አስከፊ ሕይወት እየገፋች እንደሆነ ከገጿ ለመረዳት አላዳገታትም።

"የእኔ ልጅ ሁለት ቀን፣ ሦስት ቀን ስለማትተኛ ስቃዩን አየው ነበር። ሠራተኛ እና አጋዥ ኖሮኝ የፈተነኝን በእርሷ ቦታ ሆኜ ተመለከትኩት። ለቀናት እንቅልፍ በዓይን ሳይዞር፣ በዚያ ላይ የቀን ሥራ እየሠሩ መተዳደር ከባድ ነው" ትላለች።

የምታደርገው ቢቸግራት ትምህርት ቤት እንድታስገባው መከረቻት፤ ነገር ግን በከተማው ውስጥ ትምህርት ቤት አልነበረም።

አዲስ አበባ ወዳሉ ማዕከላት በመደወልም ልጁን እንዲቀበሉላት በመጠየቅ ልትረዳት ሞክራ ነበር፤ ይህም አልተሳካም። "ቦታ የለም፤ ወረፋ ይዘው የሚጠባበቁ በርካቶች ናቸው" የሚል መልስ ነበር ያገኘችው።

በሁኔታው ልቧ የተነካው ኢማን ሳትውል ሳታድር ነበር ለእነዚህ ልጆች የሚሆን ትምህርት ቤት ለመክፈት የወሰነችው።

ቤተሰቦቿ እና ባለቤቷ ግን ውሳኔዋን በቀላሉ እንዳልተቀበሉት ትናገራለች።

ቢሆንም የወሰነችበት ጉዳይ ነውና ወደ ኋላ አላለችም። እጇ ላይ በነበረው 20 ሺህ ብር ሦስት ክፍል ቤት ተከራይታ በመጀመሪያ ልጇ ስም የሰየመችውን 'ረዋን' የሕፃናት መዋያን ከፈተች።

በወቅቱ አምስት ተማሪዎች ብቻ ነበር የመጡላት። ወራቶች በጨመሩ ቁጥር የቤት ኪራይ እና የሠራተኛ ወጪን መክፈል አዳገታት። ጥረቷን የምታውቅ አሜሪካ የምትኖር ጓደኛዋ የአንድ ወር ወጪዋን ሸፈነችላት።

ይህም ግን በቂ አልነበረም።

"የማጌጥባቸውን ወርቆቼን ሸጬ የአንድ ዓመት የቤት ኪራይ ከፈልኩ" ትላለች።

ለትምህርት ቤቱ አነስተኛ የሚባለውን ገንዘብ በመክፈል ልጆቹን የሚያመጣ ወላጅ አልነበረም። በዚህ መሃል ታሪኩን የሰማች ሌላ በአሜሪካ የምትኖር ሴት የ30 ሕፃናት ልጆችን ወጪ ሸፈነችላት።

ኢማን በዚህ ሄድ መጣ በሚለው ድጋፍ እየታገዘች፤ ፈታኝ የቢሮክራሲ ሂደቶችን እያለፈች፤ ቀደም ብሎ ማዕከል ከከፈቱ ሰዎች ልምድ እየቀሰመች፤ በ2016 ዓ.ም. የኦቲዝም ማዕከል ለመክፈት የሚያስችላትን ፈቃድ አገኘች።

ሆኖም ኦቲዝም ያለባቸው ልጆችን ከተደበቁበት ጓዳ አውጥቶ ወደ ትምህርት ቤቱ ማምጣቱም ሌላ ተግዳሮት ነበር።


"የራሴን ልጅ ይዠ ቅስቀሳ ጀመርኩ . . ."


በማኅበረሰቡ ዘንድ እንደ ኦቲዝም ያሉ ሁኔታዎች በእርግማን የመጡ እንደሆነ ነው የሚታሰቡት።

በዚህ የተሳሳተ አመለካከት ምክንያትም ወላጆች ልጆቻቸውን ደብቀው ለማሳደግ ይገደዳሉ። ግንዛቤው ያላቸው ወላጆች ደግሞ ትምህርት ቤት እና ምቹ መሠረተ ልማት ባለመኖሩ ልጆቻቸውን ቤት ውስጥ ይዘው ይቀመጣሉ።

ኢማን ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤቱ እንዲልኩ ለማድረግ የራሷን ልጅ ምሳሌ በማድረግ ነበር መቀስቀስ የጀመረችው።

"ልጄን ይዣት በከተማው እዞር ነበር። ይህን የማደርገው አንድም አካላዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ጥሩ እንቅልፍ እንድታገኝ ለማስቻል፤ በሌላ በኩል ደግሞ እንዲህ ዓይነት ልጆች እንደማያሳፍሩ ለማሳየት ነው" ትላለች።

ኢማን እንደምትለው ልጇ በመንገድ ላይ ስትጮህ፣ ስትፀዳዳ፣ ልብሷን ስታወልቅ አትሸማቀቅም ነበር።

"ይቺ ልጅ የኩላሊት፣ የጉበት ወይም ሌላ በሽታ እንደሚያጋጥመው ሁሉ የጤና እክል አጋጥሟታል። ስለዚህ ከእኔ ከእናቷ በበለጠ የሚረዳት የለም" ትላለች።

በመሆኑም ወላጆች በእነዚህ ልጆቻቸው ማፈር እና መማረር እንደሌለባቸው ትመክራለች።

ችግሩን ተገንዝባ ለልጇ የምታደርግላት እገዛ ለውጥ እንዳመጣ የምትገልጸው ኢማን፣ ኦቲዝም ያለባቸው ልጆች ብዙ ነገር ማድረግ ይችላሉ፤ የተለየ ተሰጥኦም አላቸው የሚል እምነት አላት።

ይህም ነው ራሷን በእነሱ ዓለም ውስጥ እንድትከት እና ህልሟም መሠረት እንዲይዝ ያደረገው





በየቤቱ የተደበቁ ሕፃናት

እንደ ኢማን ከሆነ በአማራ ክልል ሌላ የኦቲዝም ማዕከል የለም። በመሆኑም የእርሷ ትምህርት ቤት መከፈቱን የሰሙ ወላጆች ከሩቅ አካባቢ ሳይቀር ወደ ደሴ ልጆቻቸውን ይዘው መምጣት ጀምረዋል።

"ከባቲ፣ ከመቀሌ፣ ከባሕር ዳር፣ ከአፋር እና ከሌሎችም አካባቢዎች ወላጆች ልጆቻቸውን ይዘው እየመጡ" ትላለች።

በአካባቢያቸው እንዲህ ዓይነት ማዕከል ባለመኖሩ ወደ ከተማዋ መጥተው ቤት ተከራይተው የሚኖሩ በርካታ እናቶች መኖራቸውን ትናገራለች። በእንዲህ ሁኔታ ውስጥ ላሉ ልጆቻቸው ሲሉ ሥራቸውን ትተው የተቀመጡ የሕክምና ባለሙያዎች፣ የባንክ ሠራተኞች ጭምር እንዳሉ ኢማን ትጠቅሳለች።

ይህንን የወላጆች ፍላጎት ያየችው ኢማን፣ የደሴ ከተማ አስተዳደር ቦታ እንዲሰጣት ጠይቃ ከተሰጣት በኋላ በአሜሪካ የሚኖሩ የደሴ ከተማ ተወላጆች ደግሞ አራት ክፍል ቤት አሰሩላት።

"አሁን ላይ 40 ተማሪዎች አሉን። የብዙ እናት እንባ ታብሷል፤ አንዲት እናትን እንኳን ማሳረፍ መቻል ቀላል ነገር አይደለም" ትላለች።

ሆኖም በሰለጠኑ አገራት እንደሚደረገው እንዲህ ላሉ ልጆች እንደ ትራንስፖርት እና ሌሎች መሠረታዊ አገልግሎቶች ላይ ቅድሚያ ስለማይሰጣቸው ልጆቹ ወደ ትምህርት ቤት ሲመጡ አስቸጋሪ ሁኔታን ማለፍ አለባቸው።

ትምህርት ቤቱም ለተማሪዎቹ ማመላለሻ የመሆን ተሽከርካሪ ስለሌለው ወላጆች ልጆቻቸውን ለማድረስ እና ለመመለስ እየተቸገሩ መሆናቸውን ኢማን ታነሳለች።



"ኦቲዝም የልጆች እና የወላጆች ችግር ብቻ አይደለም"

ኢማን እንደምትለው በአሁኑ ወቅት ኦቲዝም የወላጆች ጉዳይ ብቻ አይደለም። የጎረቤትም፣ የማኅበረሰብም፣ የአገርም አሳሳቢ ጉዳይ ነው።

በኦቲዝም ምክንያት እናቶች ባሎቻቸው ጥለዋቸው ይሄዳሉ። በቤተሰብ መካከል ጭቅጭቅ እና አለመግባባቶች ይፈጠራሉ። ልጆቹ ባላቸው ባህርይ የተነሳ ከጎረቤት ጋር ያለ ግንኙነት ይናጋል። በርካታ ወላጆች ለልጆቻቸው የሚሆን ማቆያ ስፍራ ስለሌለ ሥራቸውን ለማቆም ይገደዳሉ። ልጆቹም ለከፋ የጤና እክል ይዳረጋሉ።

እነዚህ ልጆች አስፈላጊው ትምህርት እና ድጋፍ አግኝተው እራሳቸውን እንዲችሉ ካልተደረገ በቤተሰብ፣ በሕብረተሰቡ ብሎም በአገር ደረጃ የራሱን ትጽእኖ ያሳድራል። የትዳር መፍረስ እና ባለሙያ ወላጆች በተለይም እናቶች ልጆቻቸውን ለመንከባከብ እና ለመጠበቅ ቤት ሲውሉ ለአገር እና ለሕዝቡ የሚኖራቸው ሚና ይጓደላል።

ነገር ግን እነዚህን ልጆች የሚያስተምሩ እና የሚደግፉ እንደ ኢማን ዓይነት ትምህርት ቤቶች ሲኖሩ ግን ወላጆች የየዕለት ተግባራቸውን ማከናወን ይችላሉ። ማኅበራዊ መስተጋብራቸውም ይጠነክራል።

የልጆቹም ሥነ ልቦናዊ እና አካላዊ ጤና ይጠበቃል። የረዋን ህልምም ይህ ነው።

ኢማን ማዕከሉ ወደ አዳሪነት ተቀይሮ እና ተስፋፍቶ ማየት ትፈልጋለች።

"ትኩረት ተሰጥቶት፣ በደንብ ተገንብቶ ማኅበረሰቡ የእኛ ነው ብሎ ቢያድግ፤ ለሚመጣው ትውልድ መደናገርን አይፈጥርም። የሰለጠኑ ባለሙያዎች ቢኖሩ፤ ለወላጆች ሥልጠና ቢሰጥ እና መሰል ተቋማት ድጋፍ ቢደረግላቸው ፍላጎቴ ነው" በማለት የወደፊት ምኞቷን እና ህልሟን ትናገራለች።

"እኔ ሟች ነኝ። ይህ የትውልድ ተቋም ነው" የምትለው ኢማን፣ በሌሎችም ቦታዎች መሰል ማዕከላት እንዲከፈቱ መነሳሻ መሆን እንደምትፈልግ ትናገራለች።



ኦቲዝም ምንድን ነው?

ኦቲዝም የአእምሮ እድገት ላይ የሚያጋጥም ውስንነት ነው። የዓለም ጤና ድርጅት ከሁለት ዓመት በፊት ባወጣው መረጃ ከ100 ሕጻናት አንዱ ለኦቲዝም የተጋለጠ ነው።

የኦቲዝም መንስኤ አካባቢያዊ እና የዘር ችግርን ጨምሮ በርካታ ምክንያቶች እንዳሉት ሳይንሳዊ መረጃዎች ያሳያሉ።

የኦቲዝም ያለባቸው ልጆች ባህርይ የተለያየ ሲሆን፣ በጊዜ ሒደትም ባህርያቸው ሊቀየር ይችላል። እንዲህ ያለው ሁኔታ ላይ ያሉ ልጆች በተግባቦት እና በማኅበራዊ ግንኙነት መቸገር የሚስተዋልባቸው ሲሆን፣ ሌሎች ደግሞ የተለየ ባህርይ እና ድርጊት ይታይባቸዋል። ለምሳሌ ከአንድ ድርጊት ወደ ሌላው ድርጊት ለመሸጋገር መቸገርን፣ ትኩረት ማጣትን፣ ስሜታዊ መሆንን መጥቀስ ይቻላል።

አንዳንድ ኦቲዝም ያለባቸው ሰዎች ራሳቸውን ችለው መኖር የሚችሉ ሲሆን፣ ሌሎች ደግሞ የዕድሜ ልክ ድጋፍ እና እንክብካቤ ያስፈልጋቸዋል።

የኦቲዝም ተጠቂዎችን ጨምሮ ሁሉም ሰው አካላዊ እና አእምሯዊ ጤናው የመጠበቅ መብት ቢኖረውም፣ የኦቲዝም ተጠቂዎች ለአድልዎ እና መገለል እንደሚዳረጉ እና መሠረታዊ የሆኑ የጤና፣ የትምህርት እና በማኅበረሰብ ውስጥ የመሳተፍ ዕድሎችን እንደሚነፈጉ ዓለም አቀፉ ተቋም ጠቅሷል።

Related Posts

የሰው ሠራሽ አስተውሎት መተግበሪያ የሆነው ዲፕሲክ በመላው ዓለም መነጋገሪያ ሆኗል። አሜሪካ ውስጥ ከቻትጂፒቲ ቀድሞ መተግበሪያው ተመራጭ የሆነ የሰው ሠራሽ አስተውሎት መተግበሪያ ለመሆን በቅቷል። የዚህ መተግበሪያ መሥራች እና ቢሊየነሩ ሊያንግ ዌንፌንግ

ዲፕሲክ-አር1 የተሰኘው ሞዴሉ የተሠራው በነባር ቴክኖሎጂ እና ማንም ሰው በነጻ ሊጠቀምበት እና ሊጋራው በሚችለው በነጻ በሚገኝ መተግበሪያ (ሶፍትዌር፣ ኦፕን ሶርስ) መሥራት እንደቻለ ተናግሯል።