የዲፕሲክ ተወዳዳሪነት

Date Published

የዲፕሲክ ተወዳዳሪነት


ዲፕሲክ-አር1 የተሰኘው ሞዴሉ የተሠራው በነባር ቴክኖሎጂ እና ማንም ሰው በነጻ ሊጠቀምበት እና ሊጋራው በሚችለው በነጻ በሚገኝ መተግበሪያ (ሶፍትዌር፣ ኦፕን ሶርስ) መሥራት እንደቻለ ተናግሯል።

'ዋየርድ' መጽሔት ግን የዲፕሲክ መሥራች የሆነው ሊያንግ ዌንፌንግ ኩባንያው ሃይ-ፍላየር የሰው ሠራሽ አስተውሎት የጀርባ አጥንት የሆኑትን ጂፒዩዎች ወይም የግራፊክስ ፕሮሰሲንግ ዩኒት በመባል የሚታወቁትን ቺፖች እያከማቸ እንደነበር ዘግቧል።

ይህም ከ10 ሺህ እስከ 50 ሺህ ሊደርስ እንደሚችል ሲል 'ኤምአይቲ ቴክኖሎጂ ሪቪው' የተሰኘው የቴክኖሎጂ መጽሄት ግምቱን አስቀምጧል።

እነዚያ ቺፖች መሠረታዊ ጥያቄዎችን ከመመለስ አንስቶ ውስብስብ የሂሳብ ቀመሮችን እስከመፍታት የሚደርሱ ከፍተኛ የሰው ሠራሽ ሞዴሎችን ለመገንባት አስፈላጊ ናቸው።

በአውሮፓውያኑ 2022 አሜሪካ የእነዚህን ከፍተኛ ኃይል ያላቸው የቴክኖሎጂ ቺፖች ለቻይና እንዳይሸጡ አገደች።

ይህ እርምጃ "ከባድ ፈተና" ነው ሲል ሊያንግ ከቻይና መገናኛ ብዙሃን ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ተናግሮ ነበር።

በምዕራቡ ዓለም ያሉ ዋና ዋና የሰው ሠራሽ አስተውሎት መተግበሪያዎች እስከ 16 ሺህ የሚገመቱ ልዩ የቴክኖሎጂ ቺፖችን ይጠቀማሉ። ዲፕሲክ በበኩሉ አር1 የተሰኘውን የሰው ሰራሽ አስተውሎት ሞዴሉን ለማዘጋት ልዩ የሚባሉ ሁለት ሺህ እና በሺዎች የሚቆጠሩ ዝቅተኛ ደረጃ ያላቸው የቴክኖሎጂ ቺፖችን በመጠቀም እንዳሰለጠነ አስታውቋል። ይህም ርካሽ አድርጎታል።

እንደ ኩባንያው ገለጻ ዲፕሲክ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ለመገንባት 5.6 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ፈጅቷል። የቻትጂፒቲ አምራቹ ኦፕንአይአይ ባለፈው ዓመት ብቻ 5 ቢሊዮን ዶላር አውጥቷል።

ቢሊየነሩ ኤሎን መስክን ጨምሮ አንዳንዶች በዚህ ዙሪያ ጥያቄ አንስተዋል። ኩባንያው ከገደቦቹ አንጻር ምን ያህል ልዩ የቴክኖሎጂ ቺፖችን እንደተጠቀመ ሊገልጽ አይችልም ሲሉም ተከራክረዋል።

የዋሽንግተን እገዳ ለቻይና የሰው ሠራሽ አስተውሎት ኢንዱስትሪ ፈተና እንዲሁም ዕድል እንደፈጠረለት ባለሙያዎች ተናግረዋል።

በሲድኒ የቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ማሪና ዣንግ "እንደ ዲፕሲክ ያሉ የቻይና ኩባንያዎችን በውስን ነገር እንዲሠሩ አስገድዷቸዋል" ብለዋል።

"እነዚህ ገደቦች ተግዳሮቶችን የሚፈጥሩ ቢሆንም፤ ከቻይና የቴክኖሎጂ ነጻነትን ከማሳካት ሰፊ የፖሊሲ ግቦች ጋር ለማጣጣም ፈጠራን አነሳስተዋል።" ሲሉ ያስረዳሉ።

የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን እና የፀሐይ ፓናሎችን ከሚያንቀሳቅሱ ባትሪዎች እስከ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ድረስ ቻይና በትልልቅ ቴክኖሎጂዎች ላይ ብዙ ገንዘብ አፍስሳለች።

ቻይናን የቴክኖሎጂ ልዕለ ኃያል ማድረግ የፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግ የረዥም ጊዜ ምኞት ሆኖ ቆይቷል። የዋሽንግተን እገዳንም ቤጂንግ በዚህ መልኩ የተቀበለችው ፈተና ሆኗል።



የተደበላለቀ አስተያየት

ዲፕሲክ ወደ ሥራ ከገባ በኋላ የበርካታ ቴክኖሎጂ ኩባንያዎች አክሲዮን ተሽመድምዷል።

ለምሳሌ የኒቪዲያ አክሲዮኖች ድርሻ ሰኞ ዕለት በተጠናቀቀው የአሜሪካ ገበያ በ17 በመቶ ቀንሷል።

ይህም የ600 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ መቀነስ ያሳየ ሲሆን በአሜሪካ የስቶክ ገበያ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ መሆኑን ብሉምበርግ አስታውቋል።

ታዋቂው አሜሪካ የሶፍትዌር መሓንዲስ ማርክ አንድሬሴን "ዲፕሲክ-አር1ን ልክ የጠፈር ውድድር የተጀመረበትን አጋጣሚ ጋር በማወዳደር "የሰው ሠራሽ አስተውሎት መተግበሪያውን ከስፑትኒክ አጋጣሚ ጋር በማወዳደር ነው ኤክስ ገጻቸው ላይ የጻፉት

የቻይናው የሰው ሰራሽ አስተውሎት መተግበሪያ በብዙዎች ዘንድ ስጋቶችን አስነስቷል።

የዲፕሲክን የፋይናንስ ዘገባ በመጥቀስ "እየሆነ ያለውን ነገር በተመለከተ እውነቱ የተደበቀ ይመስለኛል" ሲሉ አንጋፋው ተንታኝ ጂን ሙንስተር ለቢቢሲ ተናግረዋል። ድጎማ ተደርጎለታል ወይም ደግሞ የተዘገበው ቁጥሩ ትክክል ስለመሆኑ ጥያቄ እንደሚያስነሳ ገልጸዋል።

"የሰው ሰራሽ አስተውሎት መተግበሪያው በሚያስደንቅ ሁኔታ ጥሩ በመሆኑ ይህም ለማመን አዳጋች ያደርገዋል" ብለዋል።

የአውስትራሊያ የሳይንስ ሚኒስትር ኤድ ሁሲች የደህንነት ስጋቶችን ጠቁመዋል።

"በጥራት፣ በተጠቃሚ ምርጫዎች፣ በመረጃ እና በግላዊነት አስተዳደር ላይ በጊዜ ምላሽ የሚሹ ብዙ ጥያቄዎች አሉ። ስለዚያ በጣም መጠንቀቅ ያስፈልጋል። እነዚህ አይነት ጉዳዮች በጥንቃቄ መመዘን አለባቸው" ሲሉ ለኢቢሲ ተናግረዋል።

ባለፈው ሳምንት የኦፕን ኤአዩ ሳም አልትማን እና የኦራክሉ ላሪ ኤሊሰን ከፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር በመሆን ስታርጌትን ይፋ አድርገዋል።

ለኤአይአይ መሠረተ ልማት በጋራ ሽርክና እስከ 500 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ፋይናንስ የሚደረግበት፤ በቴክሳስ እና በሌሎች አካባቢዎች የመረጃ ማዕከላት የሚኖሩት እና ከ 100 ሺህ በላይ አዳዲስ የሥራ እድሎችን የሚፈጥር ፕሮጀክት ነው።

ዲፕሲክ በድንገት መምጣቱ ስለወደፊቱ የአሜሪካ የሰው ሠራሽ አስተውሎት የበላይነት እና የአሜሪካ ኩባንያዎች እያቀዱ ስላሉት የኢንቨስትመንት መጠን ጥያቄዎችን ሊያስነሳ እንደሚችል አንዳንድ ባለሙያዎች ያምናሉ።

Related Posts

ዩናይትድ ኪንግደም እና አሜሪካ አለም አቀፉን የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (ሰው ሰራሽ አስተውሎት) ስምምነት አንፈርምም አሉ። ፈረንሳይ፣ ቻይና እና ህንድን ጨምሮ በርካታ አገራት በዚህ ጉባኤ ላይ የተደረሰውን ይህንን ስምምነት የፈረሙ ሲሆን

የሰው ሠራሽ አስተውሎት መተግበሪያ የሆነው ዲፕሲክ በመላው ዓለም መነጋገሪያ ሆኗል። አሜሪካ ውስጥ ከቻትጂፒቲ ቀድሞ መተግበሪያው ተመራጭ የሆነ የሰው ሠራሽ አስተውሎት መተግበሪያ ለመሆን በቅቷል። የዚህ መተግበሪያ መሥራች እና ቢሊየነሩ ሊያንግ ዌንፌንግ

ባለፉት አምስት ዓመታት የነዳጅ ዋጋ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል። መንግሥት በየወሩ መጀመሪያ ላይ በአገሪቱ የሚኖረውን የነዳጅ መሸጫ ዋጋን ይፋ ያደርጋል። ይህ ተመንም አንዳንድ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ ጭማሪ ሲያሳይ ሌላ ጊዜ ደግሞ ባለበት ሲቀጥል የቆየ ሲሆን