የዓለም መነጋገሪያ ከሆነው ዲፕሲክ ጀርባ ያለው ሊያንግ ዌንፌግ ማን ነው?
Author
selam
Date Published

የዓለም መነጋገሪያ ከሆነው ዲፕሲክ ጀርባ ያለው ሊያንግ ዌንፌግ ማን ነው?
የሰው ሠራሽ አስተውሎት መተግበሪያ የሆነው ዲፕሲክ በመላው ዓለም መነጋገሪያ ሆኗል።
አሜሪካ ውስጥ ከቻትጂፒቲ ቀድሞ መተግበሪያው ተመራጭ የሆነ የሰው ሠራሽ አስተውሎት መተግበሪያ ለመሆን በቅቷል።
የዚህ መተግበሪያ መሥራች እና ቢሊየነሩ ሊያንግ ዌንፌንግ ደግሞ በአንዴ ስሙ ናኝቷል።
ዲፕሲክ ባለፈው ሳምንት ነው ወደ ሥራ የገባው።
ከተቀናቃኞቹ አንጻር በርካሽ ዋጋ ለገበያ የበቃ የሰው ሠራሽ አስተውሎት መተግበሪያ ሆኗል።
የተፎካካሪዎቹን ዋጋ እያሳጣ በርካታ ጥያቄዎችን ለመጫር በቅቷል።
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአዲሱ መተግበሪያ ክስተት ለአሜሪካ የቴክኖሎጂ ተቋማት "የማንቂያ ደወል" ነው ሲሉ የደቀነውን ፉክክር ገልጸውታል።
"ጎበዙ ዌንፌንግ"
ዲፕሲክ የተመሠረተው በአውሮፓውያኑ 2023 ነው።
መሥራቹ ሊያንግ ዌንፌንግ በቀጣዩ ዓመት የመጀመሪያውን ትልቁን የሰው ሠራሽ አስተውሎት የቋንቋ አምሳል አቀረበ።
ስለ መሥራቹ የ40 ዓመቱ ሊያንግ ብዙም የሚታወቅ ነገር የለም።
የተወለደው በደቡብ ቻይና ጓንግዶንግ ግዛት ነው።
ዚሄጂያንግ ከተሰኘው ዩኒቨርሲቲ በኤሌክትሮኒክስ ኢንፎርሜሽን ምህንድስና እንዲሁም በኮምፒዩተር ሳይንስ ተመርቋል።
ቴክኖሎጂ ላይ በሚያተኩረው 36ኬአር ላይ በወጣ ጽሑፍ የሚያውቁት ሰዎች "እንደ አለቃ ሳይሆን እንደ በዕውቀት እንደመጠቀ ጎብዝ" እንደሚያዩት ገልጸዋል።
አልፎ አልፎ ብቻ በአደባባይ የሚታየው እና አንዳንዴ ብቻ ቃለመጠይቆችን የሚሰጠው ሊያንግ፣ አሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ ትኩረት አግኝቷል።
ከአገሪቱ ሁለተኛ ሰው ሊ ኪያንግ በተሳተፉበት የሥራ ፈጣሪዎች ስብሰባ ላይ እንዲገኝ የተመረጠ ብቸኛው የሰው ሠራሽ አስተውሎት ኩባንያ መሪ ነበር።
አብዛኛዎቹ የአሜሪካ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ኩባንያ መሪዎች መነሻቸው ሲሊከን ቫሊ ነው። ሊያንግ ግን መነሻው በፋይናንስ ዘርፍ ነው።
የኢንቨስትመንት ውሳኔዎችን ለማስተላለፍ ሰው ሠራሽ አስተውሎትን ተጠቅሞ የፋይናንስ መረጃን የሚተነትነው የሃይ-ፍላየር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ነበር።

ሃይ-ፍላየር እአአ በ2019 ቻይና ውስጥ ከ13 ሚሊዮን ዶላር በላይ ማሰበሳብ የቻለ ድርጅት ነው።
ሊያንግ ሃይ-ፍላየር እያለ የአክሲዮን ዋጋዎችን ሊነኩ የሚችሉ አካሄዶችን ለመለየት ሰው ሠራሽ አስተውሎት እና አልጎሪዝምን (ስልተ ቀመር) በመጠቀም ሃብት አካብቷል።
በሰው ሠራሽ አስተውሎት ዲዛይን የተደረጉ ኤች800 የኮምፕውተር ቺፖች (ግብዓቶችን) እንዲሁም በዎል ስትሪት ተወዳጅ የሆነውን ኒቪዲያን በመጠቀም በአክሲዮኖች ግብይት ላይ የተካነ ሆነ።
በአውሮፓውያኑ 2023 ደግሞ ዲፕሲክን አቋቋመ። በዚህም የሰው አዕምሮን የሚስተካከል ሰው ሠራሽ አስተውሎትን ለማዳበር ያለውን ፍላጎት አሳወቀ።
በዲፕሲክ ጥናት ውስጥ በግሉ የተሳተፈው ሊያንግ ከተለያዩ ኢንቨስተሮች የተሰበሰበ ገንዘብ (ሄጅ ፈንድ) ያገኘውን ገቢ በሰው ሠራሽ አስተውሎት ዘርፍ ምርጥ ተሰጥኦ ላላቸው ከፍተኛ ደመወዝ ለመክፈል እንደተጠቀመበትም ይነገራል።
ኩባንያው ከአሜሪካ ተቋማት ባለሙያዎችን ከመቅጠር ይልቅ እንደ ፔኪንግ፣ ስንጉዋ እና ቤይሃንግ ዩኒቨርሲቲዎች ካሉ ከቻይና ምርት የትምህርት ተቋማት የተወጣጡ ዶክትሬት ያላቸውን ምሑራንን አሰባስቧል።
የቲክ ቶክ ባለቤት እንደሆነው ባይትዳንስ ሁሉ ዲፕሲክም በቻይና ውስጥ ላሉ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ባለሙያዎች ከፍተኛ ደመወዝ ነው የሚከፍላቸው። የተቋሙ ቢሮዎች በሃንግዡ እና ቤይጂንግ ይገኛሉ።
ባለፈው ዓመት ከሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ሊያንግ ኩባንያው "ከባሕር ማዶ የተመለሱ ባለሙያዎችን አላካተተም። ሁሉም የአገር ውስጥ ባለሙያዎች ናቸው. . .እኛ የራሳችንን ከፍተኛ አቅም ማዳበር አለብን" ብሏል።
የቻይናው ሰው ሠራሽ አስተውሎት ዘርፍ "ለዘላለም የሌሎች ተከታይ ሆኖ ሊቀጥል አይችልም" ሲልም ሊያንግ ተናግሯል።
የዲፕሲክ ሞዴል በሲልከን ቫሊ አግራሞት የፈጠረበትን ምክንያት የተጠየቀው ሊያንግ "እነሱን ያስገረማቸው የቻይና ኩባንያ መድረኩን በመከተል ሳይሆን እንደ ፈጣሪ ሲቀላቀል በማየታቸው ነው። አብዛኞቹ የቻይና ኩባንያዎች የተለመዱት ሌሎችን በመከተል ነው" ብሏል።
Related Posts

No image available
